Σάββατο 28 Σεπτεμβρίου 2019

ትዳርና የቤተሰብ ኑሮ (2)

 

የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሰባት ስብከቶች ስለ ወንድ እና ሴት፡የትዳር ሕይወትና የትዳር ላይ ጥቃት
 
ዝግጅት በ: ሮ. ኢ.፣ ፍ. አ.፣ እ. ገ


 

3.  የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን ኦርቶዶክሳዊ ሥራዎች

ኦርቶዶክስ ማለት በበዓለ አምሳ ለሐዋርያት የተገለጠው ቀጥተኛ (ኦርቶ) የሆነ እምነት (ዶክሳ) ነው፡፡ ከዚህ እምነት ውስጥ የተወሰነው በቅዱሳት መጻሕፍት የሰፈረ ሲሆን፤ በኦርቶዶክሳዊ ትውፊት መሠረት ግን በቅዱሳት መጻሕፍት ከሰፈረው ባልተናነሰ መልኩ ቤተክርስቲያን በዘመናት ውስጥ ባለፈችበት ሂደት እና በቅዱሳኑ ሕይወት በኩል የተገለጸው ኦርቶዶክሳዊ ትውፊትም እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ቅዱሳን መጻሕፍት የክርስቲያናዊ ትውፊትን አስፈላጊነት የሚገልጹ ሲሆን ክርስቲያናዊ ትውፊት ደግሞ የቅዱሳን መጻሕፍትን ትምህርት እና አስፈላጊነት ያጸናል፡፡ ይህ ቅዱስ ትውፊት ሳይበረዝ በቤተክርስቲያን በኩል ከክርስቶስ እንደተቀበልነው ሆኖ የሚገኝ ነው፡፡ ይህም ትውፊት የኦርቶዶክሳውያን አባቶች አስተምህሮን፣ የቤተክርስቲያን ጉባኤያት ውሳኔዎችን[1] እና በአጠቃላይ የቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ሕይወትን የቀረጹ ነገሮችን የሚያጠቃልል ነው፡፡

የዚህ ኦርቶዶክሳዊ ትውፊት ማዕከል ላይም የምናገኘው በአዳምና ሔዋን አለመታዘዝ ምክንያት የተከሰተውን ውድቀት ተከትሎ የመጣውን የባሕርይ መጎስቆል ለማዳን የሚያስችለውን የነገረ-ድኅነት ትምህርት ነው፡፡ በዚህ ትውፊት መሠረት የመጀመሪያዎቹ ሰዎች አዳም እና ሔዋን በእግዚአብሔር መልክ እና አምሳል የተፈጠሩ ቢሆንም ባለመታዘዛቸው ምክንያት ይህንን አምሳል መጠበቅ አልቻሉም፡፡ ኦርቶዶክሳውያንም ከእግዚብሔር ጋር ኅብረት በመፍጠር እንዲለብሱ የተጠሩትም ይህንኑ አምሳል ነው፡፡ በዚህ ትግል ውስጥ ኦርቶዶክሳውያን የውድቀት መዘዝ የሆነውን ወደ ኃጢአት የሚያዘነብል ማንነታቸውን (ሥጋዊ ፍላጎቶች፣ ዘረመላዊ ዝንባሌዎች፣ መልካም ያልሆኑ ጠባዮች…ወዘተ) መጋፈጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህንን ትግል ከባድ የሚያደርገው ደግሞ በእግዚአብሔር ላይ ያመጸው እና የሰው ልጅ ዘለዓለማዊ ጠላት በሆነው ሰይጣን እና ጭፍሮቹ የሚኖረው ፈተና ነው፡፡

የኦርቶዶክስ አማኞች ወደ ኃጢያት የሚያዘነብለውን ባሕርይ በጸሎት፣ ምናኔ እና ኦርቶዶክሳዊ አስተሳሰብ (ፍሮኒማ) በማጎልበት እንዲዋጉት የተጠሩ ናቸው፡፡ የዚህ ውጊያ የመጨረሻ ግቡም ከእግዚአብሔር ጋር ከሚኖር ኅብረት የሚመነጭ ጭምትነትን እና ፍቅርን ገንዘብ ማድረግ ነው፡፡ ሊቁ ማክሲሞስ እንደሚገልጸውም የፈውሱ መንገድ ንጹሕ መሆን (Purification)፣ ከመንፈስ ቅዱስ የሆነ አብርሆት (Enlightenment) እና እግዚአብሔርን መምሰል (Theosis)
[2] ነው፡፡ ምዕመኑ በመንጻት ሂደት ውስጥ ሲያልፍ አብርሆትን ማግኘት እና ምሥጢራትን ከእግዚአብሔር በተገለጠለት ልክ መረዳት ይጀምራል፡፡ ይህም ልቦናን[3] የእግዚአብሔርን ጸጋ እና ጥበብ ለመቀበል የተነቃቃ ያደርገዋል፡፡ ይህንንም ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የመገለጥ ነገረ-መለኮት [noetic theology] ትለዋልች፡፡ በሌላ አገላለጽ፤ ነገረ-መለኮታዊ መገለጡ የቆመው በአመክንዮአዊ አረዳድ እና አእምሯዊ ጥበብ ሳይሆን በልቦና ንቃት እና ማስተዋል ላይ ነው፡፡

የዚህ የመገለጥ ነገረ-ድኅነት እና ነገረ-መለኮታዊ አስተምህሮ እንደሚያመለክተው ከሆነ ሴቶች ከዚህ ቅዱስ ትውፊት ውስጥ ቦታ ለመነፈጋቸው በቂ ምክንያት እንደሌለ ነው፡፡ እንዲያውም ሐዋርያዊ ትውፊትን በመጠበቅ እና በመያዝ ደረጃ የሴቶች ድርሻ ከፍተኛ ነበር፡፡ የዚህ ጽሑፍ አንባቢዎችም በታሪክ ውስጥ ብዙውን ነገረ-መለኮታዊ ገለጻዎች ያደረጉት ወንዶች መሆናቸውን ተመሥርተው ነገረ-መለኮት በጾታዊ ማንነት ላይ መሠረቱን የጣለ እንደሆነ ማሰብ የለባቸውም፤ ይህ የሆነበት ቤተክርስቲያናዊ፣ ማኅበረሰባዊ እና ባህላዊ ምክንያት አለውና፡፡[4] የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በታሪክ ውስጥ ሴቶችም ሆነ ወንዶች ቅዱሳንን እና ነቢያትን እንደምትዘክር፣ አልፎም ደግሞ ቅድስት ድንግል ማርያም ‹ቅድስተ ቅዱሳን› መሆኗ እንደምታምን የታወቀ ነው፡፡ በተጨማሪም ቅዱሳን ሴቶች ነገረ-መለኮታዊ አስተምህሮን ፍጹም በሆነ ኦርቶዶክሳዊ አረዳድ ለቅዱሳን አባቶች ሰማያዊ ምሥጢራትን ያስረዱበት ሁኔታ እንደነበረ[5] እና በካህናት መካክል የነበሩ ዶግማዊ [አስተምህሯዊ] ጉዳዮችን የወሰኑበት ሁኔታ እንደነበር ከታሪክ እንረዳለን፡፡[6]


የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ትምህርቶች ሲነበቡ በትርጓሜዎቹ ደጋግሞ ባስተጋባው እና ባስረገጠው ኦርቶዶክሳዊ በሆነው የዓለም አተያይ መሆን ይኖርበታል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በሐዋርያት ትምህርት ላይ ተመሥርቶ የወንዶች እና ሴቶችን መንፈሳዊ እኩልነት አስተምሯል፤ በዚህም ሴቶች ለቤታቸው፣ ለባላቸው እና ለቤተሰቦቻቸው መንፈሳዊ ተሐድሶን እንዲፈጥሩ የሚያደርግ አቅምን አጎናጽፏቸዋል[7]፡፡ ሆኖም ግን ትምህርቶቹ በሚነበቡበት ጊዜ ከተገቢው ታሪካዊ ዐውድ አንጻር እና በወቅቱ ከነበረው ከምዕመናን እና በተለይ ከሴቶች ነባራዊ ሁኔታ ተነጥሎ መታየት የለበትም፡፡[8] ከአባታዊ ርሕራሄው በመነጨ መልኩ በወቅቱ የሚያስተላልፈው መልእክት ለሰሚው የተመቸ እና አሳማኝ እንዲሆን ወቅቱን ማዕከል ያደረገ ቋንቋ፣ አገላለጽ እና የንግግር ዘይቤ መጠቀሙንም ማወቅ ይኖርብናል፡፡[9]

በኦርቶዶክሳዊ አስተሳሰብ (ፍሮኒማ) ሁኔታዎችን መቃኘት ማለት ሊቃውንት ፍጹም የማይስቱ [Infallible] አለመሆናቸውን - በአስተምህሮዎቻቸው መካከል እርስ በእርስ መስማማት መኖር እንዳለበት እና አልፎም ደግሞ አስተምህሮዎቻቸው ከሐዋርያትን ትምህርት ጋር የማይጣረሱ መሆን እንዳለባቸው መገንዘብ ነው፡፡ በሌሎች ዶግማዊ ወይም ነገረ-መለኮታዊ ባልሆኑ ጉዳዮች ላይ ግን የቅዱሳን አባቶች አስተምህሮ በምክር ለጋሽነት ሊወሰድ የሚገባ ነው፡፡ እነዚህ ምክር ለጋሽ አስተምህሮዎች በሕይወታቸው መቃኘት የኦርቶዶክሳዊ ምእመናን የግል ምርጫቸው[10] ነው፡፡ በኦርቶዶክሳዊ አስተሳሰብ (ፍሮኒማ) መረዳት ማለት ታዲያ ቀደም ብለን የተረዳናቸውን የኦርቶዶክሳዊ ትውፊት ጠባዮች እና በትርጓሜ ዙሪያ ያሉ እይታዎችን መረዳት ማለት ነው፡፡ በእርግጥ ትውፊቱ የቤተክርስቲያን አባቶችንም ሆነ ሐዋርያዊ ትውፊቱን ጠብቀው የጻፉ ዘመናዊ ሊቃውንትን ጽሑፎች በማንበብ መረዳት ቢቻልም፤ ይህ ንባብ ግን በቤተክርስቲያን ውስጥ በሚኖር ተግባር ተኮር ሕይወት ካልተደገፈ በስተቀር በጉዳዩ ዙሪያ ጥሩ የሆነ አረዳድ አይኖርም፡፡ የዚህ ጥናት ጸሐፊም የምታቀርበው እይታ በኦርቶዶክሳዊ ሥርዓት (ኑሮ) ውስጥ በማለፍ እና በማጥናት ያካበተችው መሆኑን ማጤን መልካም ይሆናል፡፡[11]



[1] ለዚህ ማሳያ የሚሆነው የቅዱሳን አባቶች ትውፊት እና የቤተክርስቲያኒቷ ሲኖዶሳዊ የጉባኤ ውሳኔዎች ናቸው፡፡ እነዚህ የጉባኤ ውሳኔዎች ተቀባይነት ያላቸው በተሳተፉባቸው አባቶች ምክንያት ነው፡፡ እነዚህ አባቶች በእምነታቸው በመጽናት እና ሃዋርያዊ አስተምህሮን በመጠበቅ ቅድስናቸውን አስመስክረዋል፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ተግሳጾችም ቢሆኑ ተቀባይ ሊሆኑ የቻሉት እርሱ አንደበ-ርቱዕ ተናጋሪ ስለነበረ ሳይሆን በእርሱ ውስጥ ባደረው የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ አማካኝነት የሃዋርያት ትምህርትን ጠብቆ በማስተማሩ ነው፡፡
 
[2] θέωσις’; የሚለው ሲተረጎም ‹አምላካዊ ማድረግ› ወይም ‹እግዚአብሔርን መምሰል› ማለት ነው፡፡
 
[3]νοῦς’; ማለት የሰው ልጅ ነፍስ ማዕከል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፤ በዚህም ከአእምሮ ይለያል፡፡የነፍስ ዓይን ተብሎም ይጠራል፡፡
 
[4] የዚህ ዋነኛ ምክንያት በቀደምት ማኅበረሰቦች ውስጥ ወንዶች ከፍ ያለ እርከንን ይዘው እንደነበር እና ሴቶች ደግሞ በአጠቃላይ የቤት ሥራዎች እና ልጅ ማሳደግ ላይ ያተኩሩ እንደነበር በማጤን የሚፈታ ነው፡፡ በተጨማሪም በኦርቶዶክስ አስተምህሮ መሠረት የክህነት ቦታን ሸፍኖ የሚያገለግለው ወንድ በመሆኑ እንደ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አይነት ብዙ የሚጽፉ አባቶች እንዲወጡ ምክንያት ሆኗል፡፡ ሆኖም ግን የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የክህነት ቦታን ለወንዶች የምትሰጠው የወንድ ልጅ የበላይነትን ስለምትቀበል ሳይሆን ራሱን በቻለ ነገረ-መለኮታዊ ምክንያት ነው፡፡ ይህ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ ኦርቶዶክስ ሊቃውንት ዘንድ መወያያ ርዕስ ሆኗል፡፡
 
[5] ይህ በግልጽ የሚታየው ቅድስት ማክሪና ከወንድሟ ከቅዱስ ጎርጎሪዎስ ዘኑሲስ ጋር ነፍስን በተመለከተ ያደረገችው ውይይት ነው፡፡ ይህ ወይይት ቅዱስ ጎርጎሪዎስ እንደቀደሞው ሁሉ በእምነቱ ጠንክሮ እንዲጓዝ ረድቶታል፡፡ ቅድስት ማክሪናንም መምህሩ እንደሆነች ያስብ ነበር፡፡
 
[6] ይህ በአራተኛው የኬልቄዶን ጉባኤ (451 ዓ.ም) ላይ የታየ ሲሆን፤ በነገረ-ክርስቶስ ዙሪያ የተወሰነው የመጨረሻ ውሳኔ የተወሰነው በቅድስት ኢውቴሚያ ተዓምር ነበር፡፡

[7] የሚከተለውን ምንጭ ይመልከቱ፡- David C. Ford, Women and Men in the Early Church: The Full Views of St. Chrysostom (South Canaan, Pennsylvania: St. Tikhons Seminary Press, 1996).
 
[8] የሚከተለውን ምንጭ ይመልከቱ፡- Deborah F. Sawyer, Women and Religion in the First Christian Centuries (New York: Routledge, 1996).
 
[9] ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሴቶች ከወንዶች አንጻር ደካማ ስለመሆናቸው እና ለእርዳታ ዝቅ ማለት እንደሚኖርብን ማስተማሩ የሚካድ አይደለም፡፡ (In Epistulam ad Ephesios, Homily 20). በተለያዩ ቦታዎችም ሴቶች የበለጠ ወሬኛ እና ብስለት የጎደለው መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡ (De Virginitate, Paragraph 40). እነዚህ ቃላቶች በቀደምት ጊዜ ከነበረው የሴቶች ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ሊቃኝ ይገባዋል፡፡ ከክርስትና በፊት በነበሩ ጊዜያት ሴቶች ከወንዶች ያነሱ ተደርገው ይታዩ ስለነበር፤ ሃሳባቸውን ሊሞርዱበት የሚችል ትምህርት የሚያገኙበት እድል እጅግ ዝቅተኛ ነበር፤ ይሄም ደግሞ ብስለት የጎደለው ስለመሆናቸው የሚታሰበው እንዲጸና የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ሆኖም ግን ቅዱስ ዮሐንስ ይህንን ስለሴቶች ቢናገርም፤ ወንዶችም ቢሆኑ ተናዳጅ፣ ትዕቢተኛ እና ግፈኛ ስለመሆናቸው ተናግሯል፡፡ (De Virginitate, Paragraph 40). በዚህ መንገድ በመናገርም ወንዶችም ሆነ ሴቶች በትዳር ውስጥ የአንዳቸውን ችግር ተረድተው የትዳር ነገረ-ድኅነታዊ ዓላማ የሆነውን ሕብረት እንዲያሳኩ የሚረዳቸውን ክርስቲያናዊ አካሄድ እንዲያዳብሩ ለማድረግ ሞክሯል፡፡ የሚከተለውን ምንጭ ይመልከቱ፡- “Ο Άγιος Ιωάννης ο Χρυσόστομος και η Οικογενειακή Ζωή του Αρχιμ. Εφραίμ, Καθηγούμενου Ιεράς Μεγίστης Μονής Βατοπαιδίου. Πηγή: Περιοδικό ‘Πεμπτουσία’ Νο 25,” republished by OODE, April 18, 2008, http://www.oodegr.com/oode/koinwnia/oikogeneia/xrysost_oikog_zwi1.htm).
 
[10]διάκρισις’; የሚለው ቃል ትርጓሜ ‹መለየት መቻል› የሚል ነው፡፡ ይህም በጸሎት እና በምናኔ ሕይወት የሚመጣ ነው፡፡
 
[11] የዚህ ጥናት ጸሐፊ የተወለደችው በሞልዶቫ ሪፐብሊክ ሲሆን ያደገችውና የተማረችው ደግሞ በግሪክ ነው፡፡ ሁለቱም ሀገሮች ኦርቶዶክሳዊ ምዕመናንን በሰፊው የያዙ ናቸው፡፡
 

ምዕራፍ 2 ወደ ይዘቶች ተመለስ ምዕራፍ 4
 
በእንግሊዝኛ ማየት ይችላሉ ፡፡
International Women's Day : Women in the Orthodox Church...
African Women (tag)
Orthodox Women Saints
Womens' Orthodox Blogs
Male and Female Created He Them...
  

 

Δεν υπάρχουν σχόλια:

Δημοσίευση σχολίου